
ዶ/ር አደይ ጸጋዬ
የሕይወት ታሪክ አደይ ጸጋዬ የወይዘሮ ላቀች ቢተውና የእውቁ ባለቅኔና ጸሐፌ ተውኔት ሎሬት ጸጋዬ ገብረመድኅን የመጨረሻ ልጅ እ. ኤ. አ. ሴፕቴምበር 10, 1974 ተወለደች። የክረምቱን የዝናብ ወራት ፍጻሜ በሚያበስሩት፣ ሜዳና ተራራውን ብሩህ ቢጫ ምንጣፍ አልብሰው በሚያስውቡትና የአዲስ ዓመት መባቻ ምልክት በሆኑት አበባዎች ስያሜም አደይ ተባለች። ከመዋእለ ሕጻናት ጀምሮም እስከ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን በሳንፈርድ የእንግሊዝ ትምህርት ቤት ከበርካታ የአፍሪካና ከሌሎች የዓለማችን ክፍሎች ከመጡ ተማሪዎች ጋር ተምራ አጠናቀቀች። አደይ ከመደበኛ ትምህርት ውጭ በተለያዩ የትምህርት ቤቱ ክለቦች ትሳተፍ ነበር። ወደ ኒውዮርክ ከመጣች በኋላ በኩዊንስ ኮሌጅ ትምህርቷን ቀጥላ በባዮሎጂ የመጀመሪያ ዲግሪዋን ተቀበለች። ከዚያም በመቀጠል በከኔቲከት ዩኒቨርሲቲ የህክምና ሳይንስ ተምራ በውስጥ ደዌና በሳንባ ህክምና ሙያ ማንሃታን ውስጥ ከሚገኘው ቤት እስራኤል የህክምና ማዕከል ሰለጠነች።
አደይ ሙያዋን የተካነችና ለታላቅ የህክምና አገልግሎት የተጠራች ነበረች። ደቡብ ብሮንክስ ባለው የቅዱስ ባርናባስ ሆስፒታል የጽኑ ሕሙማን ማቆያ መስራት ጀምራ ከዚያም በሎንግ አይላንድ ጅዊሽ የህክምና ማዕከልና በኖርዝ ሾር ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል በሳንባ ህክምናና የእንቅልፍ ህክምና (sleep medicine) ሙያ ተቀጥራ ማገልገል ጀመረች። ከዚህም በተጨማሪ ሆፍስትራ/ ኖርዝዌል ከሚገኘው ዛከር የሕክምና ትምህርት ኮሌጅ በረዳት ፕሮፌሰርነት ሰርታለች። እ ኤ አ በ2019 የሎንግ አይላንድ ጁዊሽ የህክምና ማዕከል የጽኑ ሕሙማን ክፍል ዳይሬክተር ከሆነች ከአንድ ዓመት በኋላ የኒውዮርክ ከተማ የኮቪድ ወረርሽኝ ዋና መናኸሪያ ሲሆን አደይ የሆስፒታሉን የነፍስ አድን ፍልሚያ በማስተባበርና በመምራቷ የኒውዮርክ ታይምስ፣ ወል ስትሪት ጆርናልና 60 ሚነትስ የተሰኘው የሲ ቢ ኤስ ቴሌቪዢን ገድሎቿን በመዘከር እውቅና ሰጥተዋታል።
አደይ በሳንባ ህክምናና በነፍስ አድን መድሐኒት ባሳየችው ብቃትና ባካፈለችው እውቀቷ የአሜሪካ የሳንባ ሐኪሞች ኮሌጅ አወድሷታል። ኧልትራሶኖግራፊ የተባለውን የሳንባ ደዌ ህሙማን መመርመሪያ መሳሪያ በተለዬ ችሎታ መጠቀም በመቻሏ ያካበተችውን ልምድም በተለያዩ የኒውዮርክ፣ የአሜሪካና የዓለም አቀፍ ስልጠናዎች ለሚሳተፉ ባለሙያዎች አካፍላለች። ከዚህም ባሻገር አደይ ለምርምርና ለፖሊሲ አርቃቂዎች እውቀቷን አበርክታለች፤ ስራዎቿም “አሜሪካን ጆርናል ኦቭ ሪስፓይራቶሪ ኤንድ ክሪቲካል ኬር ሜዲሲን ኤንድ ቼስት” በመሰሉ ታዋቂ መጽሔቶች ታትመዋል። የተዋጣላትና በአራት የሕክምና ዘርፍ ሙያ የበለጸገችው አደይ ከያያ ዓመታት በላይ በሕክምና አገልግሎት አሳልፋለች። በስራ መስኳና በግል ሕይወቷ፣ አደይ አዛኝና ለሌሎች ብርታትን መስጠት የምትችል፤ ለሕሙማን አስፈላጊውን የዕለት ከዕለት ህክምና እያደረገች ሳለችም የሕክምና ሙያ ፖሊሲንና የማህበረሰቡን ፍላጎት አሳምራ የተረዳች አስተዋይ ሰው ነበረች። በሙያዋ ያላት ትጋትና ከፍተኛ ችሎታ፤ እንዲሁም ህሙማን ሊያገኙት የሚገባውን የላቀ የህክምና ደረጃ እንዳይነፈጉ ዘወትር የምታደርገው ጥረት፣ ለምታክማቸው ህሙማን ከልብ ማሰቧና ከእነሱ አልፋም ቤተሰቦቻቸውን ጭምር ማበርታትና ማጽናናት መቻሏ ይደነቃል።
በዙከር ስኩል ኦቭ ሜዲሲን የሳንባ ህክምናና የነፍስ አድን ፌሎሺፕ ፕሮግራም ተባባሪ ዲሬክተር ሆና መስራቷ አደይ የቀሰመችውን እውቀትና ያካበተችውን ልምድ ለተተኪው ወጣት ሐኪሞች ማካፈል አጥብቃ የምትሻው ነገር የመሆኑ ምስክር ነው። በዚህ ስራዋም የወደፊት የህክምና ትምህርት እጩዎችና ጀማሪ ሐኪሞች ለሙያቸው ቀናኢ እንዲሆኑ አስችላቸዋለች። በመደበኛ የስልጠና ፕሮግራምም ሆነ የአካባቢ ነዋሪዎችን የጤና ግንዛቤ ለማዳበር በሚደረጉ የትምህርት ፕሮግራሞች አደይ በትጋት በመሳተፍ ተገቢ የእንቅልፍ ልማድንና የእንቅልፍ እጦት ችግርን በተመለከተ ያላትን ሰፊ እውቀት አጋርታለች።
በዓለም አቀፍ የጤና አገልግሎት ተደራሽነት ከነበራት ጽኑ እምነት የተነሳ ለበርካታ የህክምና ተልእኮዎች ሙያዋን ከማበርከቷም በላይ በትውልድ አገሯ በኢትዮጵያ ተከታታይ የህክምና ስልጠና ፕሮግራሞች እንዲኖሩ ትብብር ለመፍጠር ሞክራለች። በሰሜን አሜሪካ በሚገኙ በርካታ የኢትዮጵያዊ የጤና ባለሙያዎች ማህበር አባል በመሆን ካበረከተቻቸው አስተዋጽኦዎች መካክል በጥቁር አንበሳ፣ በጳውሎስና በጦር ኃይሎች ሆስፒታሎች፤ እንዲሁም በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የጽኑ ህሙማን ህክምና ክፍሎችን በማቋቋም አስተዋጽኦ አበርክታለች። ህመምተኞች የላቀ ህክምና እንዲሰጣቸውና ወጣት የጤና ባለሙያዎች አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያገኙ በሚደረገው ጥረት በግንባር ቀደምነት በተደጋጋሚ ተሳትፋለች።
በምትኖርበት በኒውዮርክ ከሚጠበቅባት ኃላፊነት በተጨማሪ በኢትዮጵያ የኮቪድ ግብረ ኃይል ተሳታፊ በመሆን በዚሁ ጉዳይ የሚወጣ ፖሊሲና የነፍስ አድን እርዳታ አሰጣጥን በተመለከተ ትልቅ ሚና ተጫውታለች። ለቤተሰቧ አደይ (አዲዬ)የምትታወሰው በደግነቷ፣ በማይበገር ጠንካራ መንፈሷና በማይናወጥ ጽናቷ ነው። ለእህትና ለወንድም ልጆቿ ደሞ ያሻቸውን የምታደርግላቸው የሚወዷት አክስታቸው ናት። አደይ በጫንቃዋ ብዙ ኃላፊነት የተሸከመች፤ በመልካምነቷና በቅንነቷ ብዙዎች ጉዳያቸውን የሚያዋዩዋት፤ ለብዙ ወዳጅ ዘመዶቿ እያንዳንዳቸውን እንደ ጠባያቸውና ልዩነታቸው የምታስተናግድ የጤና አማካሪያቸው ነበረች። እርጋታ የማይለያት አደይ፣ ሰዎችን ለበጎ አላማ የማነሳሳትና የማሰባሰብ ችሎታ ስለነበራት፣ ለችግሮች ተገቢውን መፍትሄ ከመሻትና ከማግኘት አትቦዝንም።
የማይረግብ የማወቅና የመማር ፍላጎቷ፣ ብልህነቷ፣ አስተዋይነቷ ለቀረባት ሁሉ ግልጽ ነበር። ከምትወዳቸው ነገሮች መሐል አገሮችን መጎብኘት፣ ቴያትር ማየት፣ ጥበብን ማድነቅ፣ በተንጣለለ ውቅያኖስ ውበት መመሰጥ፣ የምትወዳቸውን ምግቦች ከወዳጅ ዘመድ ጋር መቋደስ፣ የስፖርት ጨዋታዎችን መመልከትና መዚቃ ማዳመጥ ይገኛሉ። አደይ ያለፉ ትውስታዎቿን እያወሳች ስትጫወትና በሳቅ ስትፍለቀለቅ ያስተዋለ በወጉ የማያውቃት ሰው መንፈሰ ጠንካራነትን የታደለች የወዳጅ ዘመዷ የችግር ቀን ደራሽ መሆኗን ላይገነዘብ ይችላል።
አደይ ጸጋዬ በኦገስት 19 2023 በድንገተኛ የብሬይን አኑሪዝም ህመም ምክንያት ሕይወቷ አለፈ። እሷን ማጣት ለመላው ቤተሰብዋ መሪር ሃዘንን አስከትሏል። ብዙ ጓደኞቿና የስራ ባልደረባዎቿ እጅጉን አዝነዋል። እግዚአብሔር መልካምነቷንና አኩሪ ገድሎቿን እያስታወስን እንጽናና ዘንድ ብርታቱን ይስጠን።